አባ ቴዎድሮስ በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን የነበረ ግብፃዊ አባት ነው:: ተወልዶ ባደገባት የእስክንድርያ ከተማ ብሉያትንና ሐዲሳት በወቅቱ ከነበሩ አበው_ሊቃውንት ተምሯል:: ጊዜው ምንም መናፍቃን የበዙበት ቢሆን በዛው ልክ እነ ቅዱስ_እለ_እስክንድሮስና ቅዱስ_አትናቴዎስን የመሰሉ ቅዱሳን_ሊቃውንት ነበሩና ከነሱ የሚገባውን ወስዷል::

+በ340ዎቹ ዓ/ም አካባቢ ግን በምዕመናን ላይ ከባድ ችግር ደረሰ:: የወቅቱ ነገሥታት በስመ ክርስቲያን አርዮሳውያን ነበሩና ሕዝቡን ማስገደድ: አንዳንዴም የአርዮስን እምነት ያልተቀበለውን ማስገደል ጀመሩ:: በዚህ ምክንያትም ታላቁ_የኦርቶዶክስ_ጠበቃ_ቅዱስ_አትናቴዎስን ከመንበሩ አሳደዱት:: በምትኩም አርዮሳዊ ሰው ዻዻስ ተብሎ ተሾመ:: ይህን ጊዜ ነው እንግዲህ እውነተኛ እረኛ ያስፈለገው::
+በበዓቱ የነበረው አባ ቴዎድሮስ አላቅማማም::ቤተ_ክርስቲያን ትፈልገዋለችና መጻሕፍትን ገልጾ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወረ ምዕመናንን ያጸናቸው ጀመር:: መናፍቃኑን ተከራክሮ ምላሽ በማሳጣት ሕዝቡን ከኑፋቄ በመጠበቅ የሠራው ሥራ ሐዋርያዊ ቢያሰኘውም ለአርዮሳዊው ዻዻስ (ጊዮርጊስ ይባላል) ሊዋጥለት አልቻለም::
+በቁጣ ወታደሮችን ልኮ አባ ቴዎድሮስን ተቆጣው:: እንዳያስተምርም ገሰጸው:: አባ ቴዎድሮስ ግን እሺ ባለማለቱ ግርፋት ታዘዘበት::
+ወታደሮች እየተፈራረቁ ሲገርፉት ረድኤተ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበርና ከዛ ሁሉ ግርፋት አንዲቷም አካሉ ላይ አላረፈችም:: በዚህ የተበሳጨው አርዮሳዊ ዻዻስ የአባ ቴዎድሮስን እጅና እግር ከፈረስ ጋሪ በሁዋላ አስረው በኮረኮንች መንገድ ላይ በፍጥነት እንዲያሮጧቸው አዘዘ::
+ፈረሶቹ መሮጥ ሲጀምሩ የአባ ቴዎድሮስ አካሉ ይላላጥ ጀመር:: ትንሽ ቆይቶ ግን እጆቹ ተቆረጡ:: በሁዋላም ራሱ ከአንገቱ ተለይታ መንገድ ላይ ወደቀች:: አካሉ በሙሉ መሬት ላይ ተበታተነ:: እግዚአብሔር ቅድስት ነፍሱን ተቀብሎ አሳረጋት::
+ለቅዱሱም 3 አክሊል ከሰማይ ወርዶለታል:-
1.ስለ ፍጹም ምናኔውና ድንግልናው
2.ስለ ሐዋርያዊ የወንጌል አገልግሎቱ
3.ስለ ሃይማኖቱ ደሙን አፍስሷልና
"እምአባልከ ተመቲራ ለእንተ ሠረረት ርዕስ:
እግዚአብሔር አስተቄጸላ በአክሊል ሠላስ" እንዳለ መጽሐፍ::
+ምዕመናን ሥጋውን ሰብስበው በዝማሬና በማኅሌት በክብር ቀብረውታል::
=>አምላካችን ከቅዱሱ በረከት ይክፈለን::
=>ሰኔ 6 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ አባ ቴዎድሮስ ሰማዕት
2.አባ ገብረ ክርስቶስ
3."40" ሰማዕታት
=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅድስት ደብረ ቁስቁዋም
2.አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን
3.አባታችን ኖኅና እናታችን ሐይከል
4.ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ
5.ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
6.ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ
7.ቅድስት ሰሎሜ
8.አባ አርከ ሥሉስ
9.አባ ጽጌ ድንግል
10.ቅድስት አርሴማ ድንግል
=>+"+ መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ:: ሩጫውን ጨርሻለሁ:: ሃይማኖቴን ጠብቄአለሁ:: ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል:: ይህንም ጻድቅ: ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያሰረክባል:: ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም:: +"+ (2ጢሞ. 4:7)
<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>
No comments:
Post a Comment